በሽምግልና ምክንያት ልጃቸውን አፈር ማልበስ ያልቻሉት ርቱዕ አባት

እኒሁ አባት አደገ አመራ ይባላሉ። መኖሪያቸው ምዕራብ በለሳ አስዋጋሪ ቀበሌ ሲሆን ሙሉ ጊዜያቸውን ሽምግልና በተደገሰበት ዛፍ ፅላሎት ስር አይታጡም። አቶ አደገ ሽምግልናን በመጠቀም ብዙ የጥልና ክርክር ተቃርኖን በማስወገድ ዘለግ ያለ አበርክቶ አላቸው። በተለይ በጥቁር ደም (ደም መቃባት) ምድረ በለሴው ሲታወክ የተረበሸ ወገናቸውን ለመታደግ የሚቀድማቸው አልተገኘም።

እንደሚታወቀው በለሳ ጀግንነቱ አርበኝነቱ የሚያጠያይቅ ባይሆንም በርስ በርስ መዳማቱ ላይ መታማቱ አልቀረም።

“የት ልትሄድ ነው በለሳ፣ ሰሌን አልያዝክምሳ” በሚል ክፉ ብሂል በለሳ እግር ጥሎህ ከተጓዝክ መሞትህ ላይቀር መገነዣ ሰሌንህን መያዝ እንዳትረሳ የሚል ነባር የስም ጥላሸት አለ። ታዲያ ይህንን የስም ክፉ በበጎ ለመሻር በሚደረግ የገፅታ መመለስ ርብርብ አቶ አደገ በለሳ መሬት ላይ የግንባር ስጋ ሆነው ይስተዋላሉ።

በተለይም እኒሁ አባት አንድ ታሪክ የማይረሳው በለሳ ላይ ድንቅ አሻራን አትመው አልፈዋል። በትራፊክ አደጋ ለሞት የተዳረገች የዩኒቨርስቲ ተማሪ ልጃቸውን አፈር ለማልበስ ምፅዓት ሆነባቸው። ነገሩ እንዲህ ነው ሚያዚያ 19/ 2011ዓ/ም ከማክሰኝት መገንጠያ ወደ አርባያ በርከት ያሉ ተሳፋሪዎችን ጭኖ ይጓዝ የነበረ የጭነት አይሱዚ መኪና በመጓዝ ላይ እያለ ለከባድ የትራፊክ አደጋ ይዳረጋል። በአደጋውም ከተሳፋሪዎች መሀል ወዲያውኑ የ19ኙ ሕይዎት በአሰቃቂ ሁኔታ ሲያልፍ በርካቶችም ለከባድና ቀላል ጉዳት ይዳረጋሉ። የአቶ አደገ የጎንደር ዩኒቨርስቲ የማኔጅመንት ተመራቂ ተማሪ ልጃቸው በአደጋው ሕይዎታቸውን ካጡ አንዷ ሆነች። ሰላም ዘማሪው አቶ አደገ ግን ሌላ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ላይ ናቸው።

ከሚኖሩበት ቀበሌ ራቅ ብሎ ወደሚገኝ ሌላ ቀበሌ ተጉዘው የአንድ ወገናቸውን የጥል ጉድጓድ ለመድፈን እየጣሩ ነበር። የታደሙበት እርቅ ሂደቱ ባለመገባደዱ ለይደር ተቀጥሮ ርሳቸውም በዚያው ለማደር ይገደዳሉ። የርሳቸው ቤት ግን ሌላ መከራ ታውጆበታል። ተምራ ተመርቃ ትጠቅመናለች በሚል የላኳት የናፈቋት ልጃቸው መንገድ ላይ እንደወጣች ቀረች መባሉን ሰምቶ ቤቱ በከፍተኛ የሀዘን ማዕበል ተመትቷል። ወደ አቶ አደገ የተላከው መርዶ ነጋሪም ዘግይቶ በማግስት ከተቀመጡበት የዕርቅ ዛፍ የመከራ ዜናውና ይዞ ደረሰ። እንደሰሙ ወየው እያሉ ቢፋጠኑም የልጃቸው ቀብር ሊገባደድ ሲል እሪ እያሉ ደረሱ። አንድ ልብ የሚነካና አስተማሪ መልዕክትንም አስተላለፉ። እኔ ከሞቷ አማሟቷ የሚያሳዝን የገዛ ልጄን እንኳን በወግ አልቅሼ ለመቅበር ያልቻልኩበት ጥቁር ደም ሚባል ክፉ በሽታችንን ለማከም ተጉዤ ነውና እባካችሁ እኛ በኛ መጠፋፋቱን በቃ እንበለው” በማለት በዚሁ ለቅሶ ስነ ስርዓት ለታደሙት ለቀስተኞች መልዕክታቸውን በምሬት አስተላለፉ። ለቀስተኛውም ከልብ አዘነ። በጣም የሚደንቀው ተጨማሪ ጉዳይ በዚህ የትራፊክ አደጋ የተፈጠረውን ጦስ አቶ አደገ የሽማግልናው ተቀዳሚ ነገረ ፈጅ በመሆን ወገናቸውን ታደጉት። በየአካባቢው አቶ አደገን የመሰሉ ብዙ ያልተዘመረላቸው የሰላም ሐዋርያት አሉና ታላላቆችን በማክበር እንክበር!!!

ሰላማችሁ የበዛ ይሁን!!

ግዮን የዕርቀ ሰላምና ልማት ማህበር (ግዕሰልማ)

የካቲት 11/2013 ዓ.ም