ግዮን ሰላምና ልማት ማኅበር በጎንደሮች ማርያም/ብላጅግ ቀበሌ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ከአካባቢው የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ፤ በአካባቢው የቅማንት እና አማራ ወገኖች መካከል የነበረው አብሮነት ወደ ድሮው ግንኙነት ስለሚመለስበት እና በአጠቃላይ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ስለሚሰፍንበት መንገድ ጥልቅ ውይይት አድርጓል። በውይይቱም የላይ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ማለደ፤ የወረዳው የአስተዳደር ፀጥታ ኃላፊ አቶ ማንዴ ወ/ማሪያም፤ የወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዮት፣ የወረዳው የፀጥታ አካላት እና የማህበሩ አባላት ተገኝተዋል። በውይይቱም የላይ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ማለደ የወረዳው አስተዳደር ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየሰራቸው ያሉ ተግባራትን አውስተው ግዮን ሰላምና ልማት ማኅበርም እያከናወናቸው ላሉ የሰላም ግንባታ ተግባራት ምስጋና አቅርበዋል። ከጎንደሮች ማርያም ቀበሌ የተፈናቀሉ ወገኖችን መጠለያ ለመስራትና ለማቋቋም የወረዳውና የዞኑ አስተዳደር እንዲሁም ግዮን ሰላምና ልማት ማህበር የችግሩን ጥልቀት ለማሳየት በአደረጉት ሰፊ ጥረት ለተፈናቀሉ ወገኖች የክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቤት ክዳን ቆርቆሮ እንዲሰጣቸው የተፈቀደ ሲሆን ለዚህ ምላሽም ለክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምስጋና ቀርቧል። በቀጣይ አጭር ጊዜያትም የእነዚህን ወገኖች ቤት በርብርብ በመስራት በአካባቢው የተዘጋውን መንገድ ለመክፈት እና ማህበራዊ ተቋማትን ስራ ለማስጀመር፣ ህብረተሰቡ ወደ ቀደመ ማህበራዊ ግንኙነቱ ለመመለስ እና የሁለቱን ማህበረሰብ በጋራ የእርቅ መርሀ ግብር ለማካሄድ በማቀድ የነበረው ፍሬያማ እና ለአካባቢው ሰላም ስንቅ የሆነ ውይይት ተጠናቋል።







