ጃንተከል፣ ጎንደር እና ዕርቅ ቤት

ጎንደር ከተማ በሀገራችን ታሪክ 200 ዓመታትን በማዕከልነት ቆማ የአፍሪቃ ቀንድ የስልጣኔ መናገሻ ነበረች፡፡ ጎንደር የስጋና የነፍስ ውህድ በመሆን ሰላምና ፍቅር ከምትሰብክባቸው አጸዶቿ መሀል የጃንተከል ሽምግልና እንዲሁም የዕርቅ ቀየዋ ዕርቅ ቤት ይገኝበታል፡፡

የጃንተከል ባህላዊ ፍትህ

“ጃን ማለት ንጉስ ነው

ተከል ደግሞ መትከል

የቀለሱት ጎጆ ሁለቱ ተጋብተው

ይሆናል የጸና ንጉስ የተከለው (ፍሬዘር እንግዳ፣ 2010)

አጤ ፋሲል ወደ ጎንደር እንደገቡ ድንኳናቸውን በዚሁ ስፍራ በመትከላቸው ዋርካው ጃንተከል ተሰኘ፡፡ ጃንሆይ የተከሉት እንደ ማለት ነው (ሲሳይ ሳህሌ፣ ግርማይ ከበደና ዋሴ ነጋሽ 2009)፡፡ ወደ ኋላ ተጉዘን ጎንደርን ከምንዳስስበት ቋሚ ምስክሮች አንዱ የጃንተከል ዋርካ ነው፡፡ ጎንደር ሁለት መቶ ዓመታት የሀገሪቱ መናገሻ ሆና ስትዘልቅ ሙሉ ዕድሜዋን በአብሮነት ከዘለቁት መሀል ጃን ተከል አንዱ ነው፡፡

ጃንተከል ብዙ ታላላቅ ጉባዔያትን ያስተናገደ፣ ከነገስታቱ ዙፋን ችሎቶች የሚወጡ ህግጋት የሚተዋወቁበት፣ ጠላትን ለመመከት በሚደረጉ ዘመቻዎች የክተት አዋጆች የሚለፈፉበት፣ ዜና ሹመቶች የሚበሰሩበት አጸድ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የነገስታቱን ሞት መርዶ የሚደመጥበት ነባሩ ንጉስ ከዓለም በሞት መለየታቸውን “ያለነው እኛ የሞትነው እኛ” በሚል ሁለትዮሻዊ ተቃርኖን የተሸከሙትርጉም ያለው ቃልም የሚለፈፍበት ስፍራ ነበር፡፡ አዋጁ ያለነው እኛ በሚል በሞቱት ንጉስ ምትክ ሌላ ስዩም መፈጠሩን ያዘክራል፡፡ ከዚህ አዋጅ ቀጥሎም አዲሱ ንጉስ ዘውድ ደፍቶ ጃንተከል አደባባይ ጉብ ብሎ ይታያል፡፡ ህዝቡም “ይበጅልህ ያድርግልህ” እያለ የምርቃት ቡራኬውን ያቀርባል(ሲሳይ ሳህሌ፣ ግርማይ ከበደና ዋሴ ነጋሽ 2009)፡፡

ጃንተከል ሸምጋይ ፈታህያን ፍርድ የሚሰጡበት ሸንጎም ነበር፡፡ በዚህ የጃንተከል ሸንጎ የተበደለ ተክሷል የቀማ መልሷል፡፡ ይህ ዋርካ እስከዛሬ ድረስ የኪሳራ ሒሳብ እስከተወራረደበት አሁናዊ የድራፍትና ቁርጥ እልፍኝ እስከሆነበት ድረስ ሸምጋይ አባቶች ዕርቀሰላም የሚያወርዱበት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነበር፡፡ ስለዚህ ጃንተከል በአደባባይነት የተተከለ ለዕርቅ ግብር የቆመ ነበር ማለት ነው፡፡ አሁናዊ ቁመናው ግን በተዝናኖት ማዕከልነት ሰበብ ያልተገባ ከታሪኩ ጋር የሚጋጭ ቁመና ላይ መገኘቱ በዚህ ዘመን የምንገኝ ሁሉ ከታሪክ ተጠያቂነት የሚያስመልጠን ስላልሆነ ጃንተከልን ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ መረባረብ ይገባናል፡፡

ዕርቅ ቤት

አሁናዊ ታሪካቸው ከተዳፈነ እንዲሁም ስምና ግብራቸው ትይዩ ከሆነላቸው ጥንታዊ የጎንደር ከተማ ሰፈሮች መሀል ዕርቅ ቤት፣ ድብ አንበሳ፣ ቀኝ ቤት፣ አባ አብየ እግዚዕ፣ ፈረስ ቤት፣ ድንጋዬ፣ አቡን ቤት፣ እጨጌ ቤት፣ ግራ ወንበር፣ አዲስ ዓለም፣ እርግብ በር፣ ወለቃ ወዘተ…ነበሩ፡፡ ግራ ወንበርና ፊት አቦን አዋስኖ የዚያን ዘመን የዕርቅ ሽምግልና ክዋኔን ያስተናግድ የነበረ፤ ሸምጋይ አባቶች ተፈልገው የማይጠፉበት፤ የጎንደር ብስቁል ልጃገረድ ዕንባዋን አፍስሳ ለበደሏ ካሳ ለመጠየቅ አቤት ለማለት የምትገሰግስበት… የሀገር ሽማግሌዎች ቀየ “ዕርቅ ቤት” የተባለው ሰፈር ነበር፡፡ ጉዳያቸውን ሸምጋይ አባቶች እንዲፈታላቸው የሚሹ አቤት ባዮች ወደ ዚሁ መንደር አቤቱታቸውን ይዘው ይጓዙ እንደ ነበር ቃላዊ አስረጅዎቻችን ይጠቁሙናል፡፡ ከዚሁ ሰፈር ኩታ ገጠም የሚገኘው አሸዋ ሜዳም ህዝብ ተሰብስቦ የሚመክርበት መስክ ነበር ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ የጎንደር መንደሮች አሁንም ድረስ ስማቸው ሳይጠፋ ያልተቋረጠ የከተሜነት ታሪካቸውን ይዘው እንደዘልቁ ቢታወቅም ዕርቅ ቤትን ጨምሮ ብዙዎቹ ግን ከነ ስማቸው የዝንጋዔ ደለል ውጧቸው እንመለከታለን፡፡