የጠገዴ ስምንቱ ማይቤት ባህላዊ የፍትህ ስርዓት-ሌላዉ ወርቃማ ዕሴታችን

አፈ-ታረኩ እንደሚነግረን ከአንድ ሺህ ዓመት ዓለም ገደማ ከየመን ወደ ሀገር ቤት እንደገቡ የሚነገሩት ነገደ ዮቅጣን መሪያቸው ንጉስ ኢትዮጲስ ይባላል። ታዲያ ይህ ንጉስ ኢትዮጵያን አቅንቶ በስሙም አደላድሎ 55 ዓመታትን እንዳስተዳደረና አምስት ልጆችንም እንደወለደ የታሪክ መረጃዎች ይነግሩናል። ርስት ጉልት ያከፋፈላቸው አምስት ልጆቹም ሳባ ኖባ፣ በለው፣ ከለው፣ ላክንዱና ኖክ ይሰኛሉ። በመጀመሪያ ጠገዴን ለበለው አርማጭሆን ለከለው ርስት ሰጠ። ጠገዴን ያቀናው ልጅ በለውም መሀል ጠገዴ፣ ምድረ ገበታ፣ እንጣቤላ፣ ደቃ ጋሮ፣ ቆላ ወገራና ዳልዲማ በተባሉ ቦታዎች የኦሪት ቤተ መቅደሶችን በማሰራት ሕዝቡን በሕገ ኦሪት ማስተዳደር ያዘ። ስምንት ልጆችንም ወለደ። ስማቸውና ያቀኑት ርስትም …

⓵ቀራቅር- አዝማች አብርሀም

⓶ምጭዋ- አዝማች እንግዳ እግዚዕ

⓷አዴት- አዝማች ዘአማን

⓸ቻግኔ- አዝማች አግኔ

⓹ደቂ አባ- ቄስ አባ

⓺ደቀ አጋሮ- አዝማች ደረሰ ወንድ

⓻ጋሞ- አዝማች አምባኖም

⓼ ደባሽ ክንድሽ- አዝማች ዘኃዋርያት ናቸው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከወንዝ አባቱ ጠገዴ ዘወልድ ጋር ተወዳጅቶ በነኝህ ስምንት ወንድማማቾች የፀና ስምንቱ ማይ ቤት የተሰኘ የሽማግሌዎች የወል ምክር ተደነባ። ከነዚህ ወንድማማቾች ካተሙት አሻራ በተዋረድ ከስምንቱ ወንድማማቾች ዘውግ የተገኘ ባላባት የሽማግሌ ውክል እየሆነ የጉባዔው ተሳታፊ የመሆን ልዩ መብት ተሰጠው። የስምንቱ ተወካይም አጣጥበር ከተሰኘች ማዕከላዊ መገናኛ ነጥብ አጣጥ ከተሰኘ ዛፍ እግር ቁጭ ብለው ምክረ ሀሳብ ያደርጋሉ። የተጣላን ያስታርቃሉ። የተበደለን ያስክሳሉ። ደምንም ያደርቃሉ። በማዕከላዊ ዕሳቤ በህዝብና መንግስት መሀል ቆመው የተጣመመ ፍርድን እያቃኑ ተግባቦት እንዲፈጠር ያስችላሉ። በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በሀገር ግዳጅ፣ ጠገድቼው ቀድሞ እንዲሰለፍ መክረው ዕዝ ያወርዳሉ። ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የወሰኑት ያሳረፉት ውሳኔ ከአድልኦ የነፃ የይግባኝ መብትን የጠበቀ ሀገሬው አምኖ የሚቀበለው ሆነ። እነኝህ የባህላዊ ፈታሕያን መናህሪያ ክቡር የፍትህ አፀዶች ርስ በርሳቸው የተሳሰሩና ነፃ ሆነው ፍትህ ርትዕን የሚያሰፍኑ ባህላዊ ዕሴቶቻችን ናቸው። የጠገዴ ስምንቱ ቤት የሽምግልና ተቋም እስካሁን ድረስ በገቢር ላይ ፀንቶ እንደሚገኝ የጎንደሯ ቁስቋም ቤተክርስቲያን አጸዶች ላይ በአካል ተገኝተን ማረጋገጥ ችለናል። ይህንን የስምንቱ ማይ ቤት የአባቶች ምክረ ውሳኔን ጥሶ ታርቆ ያፈረሰ “ጥቁር ውሻ ይውለድ” በሚል መርገምት ቃልም እንደታሰረ ይታመናል። ማህበራችን ግዮን የዕርቀ ሰላምና ልማት ማህበር (ግዕሰልማ) እነኝህንና ሌሎች ወርቃማ ዕሴቶቻችንን መጠበቅና ወደ ቀጣይ ትውልድ ማሻገር ላይ አተኩሮ ይሰራል።

ግዮን የዕርቀ ሰላምና ልማት ማህበር (ግዕሰልማ)

ሐምሌ፣ 2014 ዓ.ም