በረዥም ዘመን ታሪክ እንዲሁም በገቢር ተፈትነው ከዳበሩ ስር የሰደደ ስርፀት ካላቸው ጎንደር አካባቢ ከሚከወኑ የሽምግልና ስነ-ስርዓትና ተግብሮት መሀል የአርማጭሆው “በአምስት” አንዱ ነው።
***
ቃላዊ አስረጅዎች እንደሚያስረዱን አርማጭሆን ቀድመው ካቀኑ ነገስታት ቀዳሚው አፄ ናኦድ ናቸው። እኒሁ ንጉስ ታዲያ ከቀናት በአንዱ ከባድ የጥል ቋጠሮ ወደ ሸንጓቸው ሲቀርብ እንዲህ አሉ የሚል ትዕውፊታዊ የቃል ነገራ አለ። “እባካችሁ እነዚህን ጥለኞች አምስት ሆናችሁ ዛፉ ስር ተቀምጣችሁ ገልግሏቸው” አሉ ይባላል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምድረ አርማጭሆ በአምስት (በባንባችን) እንሸማገል ወደ ሚል በጎ ልማድ መጥቶ ብዙ የግጭት ጉድጓዶችን ሲዘጋ ቆይቷል።
***
ከዚህ በጎ የአምስት የእርቅ ዕሴት ጋር ተዋግኖ የሚቀርብ ሌላ ተረክም አለ። በአንድ አዝማን መሀል የአርማጭሆና ጠገዴ ህዝብ የአንገረብ ወንዝ መዳረሻ ከሆነው አሳዋር ወንዝ አሳ በማስገር ሂደት በተፈጠረ እሰጣ እገባ ግራ ቀኙ ላይ የበርካታ ሰዎች ደም ፈሶ ነበር። ለጥቂት ዓመታትም ሁለቱ ሕዝቦች ቂም አርግዘው ያለ ግንኙነት ቆዩ። ከዚያም የሀገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች “የአንድ አውራ የአንድ ባዝራ” ልጆች ለምን እንዲህ በክፉ እየተፈራረጁ እየተፋጁ ይዘልቃሉ በሚል የክርስቶስ መስቀል በየአፍላጋቱ ወጥቶ ከዚያው አሳዋር ከሚባለው ወንዝ አቅራቢያ ከሚገኝ ዛፍ ስር ተቀምጠው እርቅ አወረዱ።
***
ከዚህ ታሪካዊና ባህላዊ ክዋኔ ጋር በአብሮነት የተከወነው ኩነት ሸምጋይ አባቶች ለዕርቅ የመረጡት ዛፍ ከዚያ ቀን በፊት የተለምዶ መጠሪያው በውል የማይታወቅ ነበርና ከዚሁ ዕለት ጀምሮ “ደም በቃ”(ደም ይብቃ) በሚል ደም በደም እንደማይደርቅ አበክረው የውሏቸውን ሰናይ ግብር ሊያዘክር በሚችል ዘላለማዊ ቋንቋ ደምበቃ በሚል ስዩም ቃል አትመው አልፈዋል። በየአዝማናቱ መሀል በዚህ የደም በቃ ሾላ መሰል ዛፍ ስር በርካታ የግልና የወል ቀዳዳዎች ተደፍነዋል አያሌ የጥቁር ደም መዝገቦችም ተፍቀዋል። እኛም ደም በደም አይደርቅም ደም በቃ እንላለን!!!
” ደም በደም አይደርቅም”
***
ወቅቱ ነቃ ማለትን ይሻል ሰላም!
ግዮን የዕርቀ ሰላምና ልማት ማህበር (ግዕሰልማ)
ሰኔ 2014 ዓ.ም

