ግዮን የዕርቀ ሰላምና ልማት ማህበር (ግዕሰልማ) ከሁለቱ የጎንደር ከተማ ገጠር ቀበሌዎች ማለትም ድባ ደፈጫና ፈንጠር እንዲሁም ከጎንደር ዙሪያ ወረዳ ከሚገኙ ስሆር ጉልቶችና ዳዋ ዳሞት ከተሰኙ ቀበሌ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ለሁሉም ቀበሌዎች አማካኝ በሆነችው ልዩ ስሟ “ስመ ክፉ” ትሰኝ ቦታ በመገናኘት ሰኔ 20/2014 ዓ.ም የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት በሚያሰፍን መንገድ ውይይትና የቀደመውን ግንኙነት ለመመለስ ያለመ ዝግጅት ተካሂዷል። በውይይቱም ከጎንደር ዙሪያ ወረዳ እንዲሁም ከዞብልና ማራኪ ክፍለ ከተማ የተወጣጡ አመራሮች ተሳትፎ አድርገዋል። ከአሁን ቀደም በአዋሳኝ አካባቢዎች አማራ ቅማንት በሚል ሰበብ ሌቦችና ህገወጦች ማንነትን ሽፋን አድርገው የአራቱን ቀበሌ ነዋሪዎች በሚያውክ መንገድ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ይታወሳል። ስለሆነም ከ1500 በላይ የማኅበረሰብ ክፍል በተሳተፈበት ዝግጅት የጋራ ኃላፊነትን ለመውሰድ በሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮች በጥልቀት መክሮ ህገወጦችን በማውገዝ የጋራ ሰላማቸውን በጋራ ለማስጠበቅ፤ ከአሁን በፊት ላልተው የነበሩ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ወደ ቀደመ ኑባሬያቸው እንዲመለሱ፤ የመንግስት አካላት ስመ ክፉ ላይ የጋራ የፀጥታ ግብረኃይል በማቋቋም የአካባቢውን ሰላም ወደ ዘላቂ መረጋጋት ለማምጣት በቁርጠኝነት እንዲሰራ እንዲሁም ውይይቱ በየወሩ ቀጣይነት እንዲኖረው በሚል የጋራ ተግባቦት በመፍጠር በአስደሳች ሁኔታ የዛሬው ምክክር ፍፃሜ አግኝቷል።


