ራያ በህግ አምላክ ከምትለው ‘በዘወልድ አምላክ’ ብትለው ያነሳውን ይጥላል ለጠብ የተጋበዘበትን አጋጣሚ እርግፍ አድርጎ ይተዋል የሚባለው እሙን ነው። ከመደበኛው ፍርድ ቤት እጅግ በቀለጠፈና በተሻለ መንገድ ግጭቶችን የመፍታትም ሆነ ባለመብትነትን የማረጋገጥ ልዩ አቅም ያለው የራያ ቆቦው “የዘወልድ ሽምግልና”። ራያዎች በዕፁብ ተረካቸው አንድ ትዕውፊትን ያዘክራሉ። ሰንየ ሰገድ፣ ክፍሎ፣ መዘርድ እና ዘወልድ የሚባሉ አራት ወንድማማቾች ስም የሚጠራ የወንዝ አባቶች እንደነበሯቸው ይታመናል።
በአራቱ ወንድማማች የወንዝ አባቶች ስም ፀንቶ የቆመው አራት አይነት ሽምግልና በተለያዩ የራያ ግዛቶች በየራሳቸው አውድ የራሳቸውን ሂደትና ስርዓት ይዘው በገቢር እስካሁን ዘልቀዋል። ከአራቱ ስያሜዎች ገኖ የወጣውና ከአራቱ ገዝፎ የሚስተዋለው ይሻል ዕውቅናንም ተላብሶ የቆመው ከቆቦ ዙሪያ እስከ መቅደላ ዞብል ድረስ ባለው አካባቢ የሚከወነው የዘወልድ ባህላዊ ዳኝነት ነው።
ዘወልድ ባህላዊ የሽምግልናና ዕርቅ ሥርዓት መጠሪያውን ያገኘው ለአያሌ ዘመናት በራያዎቹ መካከል የሚፈጠሩ ማንኛውንም ግጭትና አለመግባባቶች በመፍታት ይታወቁ ከነበሩት ከላስታ አካባቢ ነዋሪ ከነበሩት “ዘወልድ” ከሚባሉ ታላቅ አባት እንደሆነ ከባቢያዊ ነገራ አለ። ዘወልድ በርካታ አዝማናትን ተሻግሮ በትውልድ ቅብብሎሽ መሀል ዛሬም ድረስ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ቀለሙ የደመቀ ሆኖ ‘ሴረሞኒያል’ የሆነ የሠላም ማስጠበቂያ ባህላዊ ተቋምማችን ነው።
በንፃሬ ዘወልድ ከሌሎች የአማራ የሽምግልና ባህላዊ አደረጃጀቶች የተሻለ ተቋማዊ ቅርፅና አውድን ተላብሶ ቆሞ ይስተዋላል፡፡ የራሱ የሆነ መደበኛ አደረጃጀትን ፈጥሮ በራሱ ጥረትና በማህበረሰቡ የተሻለ ሱታፌ በተሻለ ቁመና ላይ ይገኛል። ሌላው ልዩ መገለጫው ጥልና ግጭቶችን በአጠረ ጊዜ ለእልባት ማብቃቱ ነው። የዘወልድ ሽምግልና በዛ የተባለው የጊዜ ርዝማኔ 14 ቀናት ሲሆን ከዚያ ባነሰ ጊዜም ማንኛውንም ኬዝ የመፍታት ልማድ አለው።
በቀጠሮ በይደር ባለጉዳዮችን በማጉላላት ከታመነው፤ ስልጡን ስትራቴጂ ነኝ የተሻለ አማራጭ ነኝ ከሚለው፤ ዘመናዊ ፍርድ ቤት ከዘወልድ አባቶች የቀለጠፈ ዳኝነት ሊማር በተገባው ነበር። ግን ባህላዊ በሚል ኋላ ቀሪ ዕሳቤ ‘ሞደሬት’ ነን ባዮች ወርቁን ሽምግልና ወደ መዳብ ውላጤ አመጡት። ልጅ ለናቷ ምጥ አስተማረቻት ሆነና ነገሩ የአንድ ክፍለ ዘመን ዕድሜ የማይሻገረው ዘመናዊ ፍርድ ቤታችን የሚሊኒየም ዕድሜ ጠገቡን ለባህላዊ ፍትሁ መራሒ ሙሴ ልሁንህ አለው። እንደ ዘወልድ ዓይነት የካበተ ልምድና የተሻለ ችግር ፈች የሆኑትን ባህላዊ ተቋማት ንቆ አቅሎ ማንሳት አይገባም። ማህበራችን ግዮንም ዝማኔ ላይ ነን የሚሉትን ዘመናዊ ፈታህያንን በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ‘ሎቢ’ በማድረግ ፍርድ ቤቶች ለሽምግልናው የተለየ ቦታና እውቅና እንዲሰጡ በትጋት እየሰራ ይገኛል።
” ደም በደም አይደርቅም”
ሰላማችሁ የበዛ ይሁን!!
ግዮን የዕርቀ ሰላምና ልማት ማህበር (ግዕሰልማ)
የካቲት 14/2013 ዓ.ም

