በአንድ ወቅት የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የወንድም ልጅና የእቴጌ ዘውዲቱ ባለቤት የነበሩት ራስ ጉግሳ ወሌ ደብረ ታቦር ላይ ሸንጎ ቆይተው ሲነሱ አንድ ዛፍ ስር አንዳች ክስተትን አስተዋሉ። እነዚህ ሰዎች ምን እያደረጉ ነው ግራሩ ስር የተቀመጡት? ሲሉ አብረው ያሉትን አሽከሮቻቸውን ጠየቁ። እነርሱም እነዚህማ የተቀደደን ቤት እየሰፉ ፥ የተጣሉትን እያስተረቁ ደምን እያደረቁ ነው አሏቸው። ይህንን በጎ ግብር ሲፈፅሙ ምን አግቦ አላቸው? ብለው መልሰው ጠየቁ። አግቦ ማለት የሚገባቸው ደሞዝ ምንዳ እንደማለት ነው። አረ ለክብርና ለአንክሮ እንጂ አግቦስ የላቸውም ብለው መለሱላቸው።
ራስ ጉግሳ ይህንን የሸምጋይ አባቶችን ፅኑ ልፋትና ድካም በማስተዋልና በመረዳት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እነዚህማ የኔን ሸንጎ ቀሊል የሚያረጉ ሰናያ አባቶች አደሉም እንዴ በሉ ከዛሬ ጀምሮ የብር እኩሌታ ደምዎዝ እንዲከፈላቸው በማለት ደንብን ሰርተው እንደነበር ቃላዊ ትዕውፊቶች ይናገራሉ። ግን ይህ አግቦ ወደ ዛሬ መሻገር አልቻለም። የፍንጥር ተብሎ ዕርቁ ሲፈፀም እህል ውሃ ይቀርብ ይሆናል። በእርግጥም ይህ የአማራ አባቶች ሽምግልና ያለ ራስ ጥቅም ክፍያ አልቦ ሊያውም ዕርቁ እንዲወርድ በሚል ተምኔት በባዶ ሆድ እህል ውሃ ሳይቀመስ በግጫው በጥንጫው ወለል ላይ ተቀምጠው የዕርቀ ሰላም ገቢርን ይከወናሉ። የፈሰሰ ደምን በዕርቅ ያደርቃሉ።
ሰላማችሁ የበዛ ይሁን!!
ግዮን የዕርቀ ሰላምና ልማት ማህበር (ግዕሰልማ)
ጥር 24/2013 ዓ.ም

