ታሪካዊው የደም በቃ ዛፍና የሚፈታው ቋጠሮ!

ከአርማጭሆ ማህበረሰብ በጎ የአምስት የሽምግልና ዕሴት ጋር ተዋግኖ ከሚቀርቡ ተረኮች አንዱ የደም በቃ ዛፍ ሽምግልና ነው። ጎንደር አካባቢ ኩታ ገጠምና ብዙ ህዝባዊ መስተጋብራቸው እንዲሁም ማህበረሰባዊ ስነልቡናቸው (Psycho Social) ሁነታቸው በእጅጉ ቅሩብና ምስስልነት ከሚስተዋልባቸው ነዋሪዎች አርማጭሆና ጠገዴ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ታዲያ በአንድ አዝማን መሀል የአንገረብ ወንዝ መዳረሻ ከሆነው አካባቢው ላይ አሳዋር ተብሎ በሚጠራው ወንዝ አሳ በማስገር ሂደት በተፈጠረ ዕሰጣ እገባ በሁለቱ ህዝቦች ግራ ቀኝ ላይ የበርካታ ሰዎች ደም ፈሰሰ፡፡ ለጥቂት ዓመታትም ሁለቱ ከአንድ የዘር ሀረግ እንደ ተመዘዙ የሚነገርላቸው የበለውና የከለው ህዝቦች ባልረባ ጉዳይ ደም ተቃብተው እርስ በርስ በባላጣነት ተፈራርጀው ለጥቂት ዓመታት ያለ ግንኙነት ቆዩ። ከዚያም የሀገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች በመነጋገር “የአንድ አውራ የአንድ ባዝራ” ልጆች ለምን እንዲህ በክፉ እየተፈራረጁና እየተፋጁ ይዘልቃሉ በሚል የክርስቶስ መስቀል በየአፍላጋቱ ወጥቶ ከዚያው አሳዋር ከሚባለው ወንዝ አቅራቢያ ከሚገኝ ዛፍ ስር ተቀምጠው ዕርቅ አወረዱ።

ከዚህ ታሪካዊና ባህላዊ ክዋኔ ጋር በአብሮነት የተከወነው ኩነት ሸምጋይ አባቶች ለዕርቅ የመረጡት ዛፍ ከዚያ ቀን በፊት የተለምዶ መጠሪያው በውል የማይታወቅ ነበርና ከዚሁ ዕለት ጀምሮ “ደም በቃ”(ደም ይብቃ) በሚል ደም በደም እንደማይደርቅ አበክረው የውሏቸውን ሰናይ ግብር ሊያዘክር በሚችል ዘላለማዊ ቋንቋ ደምበቃ በሚል ስዩም ቃል አትመው አልፈዋል። በየአዝማናቱ መሀል በዚህ የደም በቃ ሾላ መሰል ዛፍ ስር በርካታ የግልና የወል ከባድ ሸክሞች ቀሊል ሆነዋል፡፡ አያሌ የጥቁር ደም መዝገቦችም ተፍቀዋል። ዞጲ ግንዲላውም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ዛሬ ድረስ የፋሲል ግንብ ቀዘባ ሆኖ ይስተዋላል፡፡

ግዮን የዕርቀ ሰላምና ልማት ማህበር (ግዕሰልማ)

የካቲት 2015 ዓ.ም